ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ የሀገር ዉስጥ ተፈናቃዮችን፣ ተመላሾችን እና ጾታዊ ጥቃት ሰለባ የሆኑ ወገኖችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ዛሬ አስጀምረናል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከሚታወቅባቸዉ የማህበረሰብ አገልግሎቶች መካከል በህግ ት/ቤት በኩል የሚሰጠዉ የነጻ ህግ ድጋፍ መስጫ ማዕከል አገልግሎት አንደኛዉ ነዉ፡፡ ማዕከሉ በአንድ መልኩ ሌጋል ክሊኒክ ሆኖ የትምህርት ጥራትን ያስጠብቃል፤ በሌላ መልኩ ድምጽ ለሌላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ድምጽ በመሆን የማሕበረሰብ አገልግሎት መስጠት ነው።
ማዕከሉ በዋነኛነት አገልግሎት የሚሰጠው በሀገራችን የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች እንዲሁም የመብት ጥሰቶች ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለይ ሴቶች፣ ህፃናት፣ ሕሙማን፣ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋዉያን እና በአጠቃላይ በገንዘብ እጥረት ምክንያት ጠበቃ መግዛት የማይችሉ የሕብረተሰብ ክፍሎችን መብት የሚያስጠብቅ በመሆኑ የአገልግሎቱን ዋጋ የላቀ ያደርገዋል፡፡
ማዕከሉ በ2002 ዓ.ም ሲቋቋም አገልግሎቱን የጀመረው ጎንደር ከተማ በከፈታቸው 2 ማዕከላት ሲሆን በሂደት የማዕከላቱን ቁጥር 16 በማድረስ ወደ ብዙ ወረዳዎች በመቅረብ ተደራሽ ያልነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን መድረስ ተችሏል፡፡
በእነዚህ ማዕከላት አማካኝነት እስካሁን ከ40ሺ በላይ የሚሆኑ ተጠቃሚወችን ወክሎ ፍርድ ቤት መከራከርን ጨምሮ የተለያዩ የህግ ድጋፍ አገልግሎቶችን በነጻ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡

በ”USAID የፍትህ ተግባራት በኢትዮጵያ” ድጋፍ ዛሬ በይፋ የተመረቁት የአዘዞ እና ደባርቅ ከተሞች ነጻ የሕግ ድጋፍ መስጫ ማዕከላትም የዚሁ አካል ናቸው፡፡
“USAID የፍትህ ተግባራት በኢትዮጵያ” ከ4.5 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ ያደረገልን ሲሆን በቀጣይ አንድ ዓመት ገደማ የፕሮጀክት ቆይታ ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ የሀገር ዉስጥ ተፈናቃዮች፣ ተመላሾች እና ጾታዊ ጥቃት ሰለባ የሆኑ ከ3000 በላይ ወገኖችን ተጠቃሚ ይሆናሉ።
በገጠመን የህልውና ጦርነት ምክንያት በርካታ ወገኖቻችን የተለያዩ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የስነ ልቡና ቀውሶች የተዳረጉ በመሆኑ የእነዚህ ማዕከላት መቋቋም ፋይዳው የጎላ ነው።
የገንዘብ ድጋፍ ላደረገልን “USAID የፍትህ ተግባራት በኢትዮጵያ”፣ ፍርድ ቤቶች፣ አቃብያነ ህግ ጽ/ቤቶች፣ የፖሊስ ጽ/ቤቶች፣ ማረሚያ ቤቶች፣ ፕሮጀክት ቀርጸው ይህን ፈንድ ላመጡና ነጻ የሕግ ማዕከላችን ላለፉት 12 ዓመታት ሳይቆራረጥ ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ በመሆን ሙያዊ ግዴታቸውን ለተወጡና እየተወጡ ላሉ የህግ ት/ቤታችን መምህራንና ተማሪዎችና ባለ ድርሻ አካላት ሊመሰገኑ ይገባል።
